:::ዜናዎች:::

:::ያግኙን :::

ርዕሰ አንቀጽ

ወጣቱ ወዴት ነው መሄድ ያለበት)
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሃይማኖት ፍቅር በነደዱ፣ ለተጋድሎ ራሳቸውን በሰጡ የአባቶቻቸውን ታሪክ ለመድገም በቆረጡ ታሪክ ሠሪ ወጣቶች የተሞላ ነው፡፡ እነ አቤልን፣ እነ ይስሐቅን፣ እነ ያዕቆብን፣ ነቢዩ ዳንኤልን እና ሠለስቱ ደቂቅን፣ ባሮክን እና አቤሜሌክን በብሉይ ኪዳን እናገኛቸዋለን፡፡Ý
ተጨማሪ

 
 
  ራእይ
 
የጥያቄዎ መልስ
  ሊቀ ጳጳሱን ይጠይቁ
 
 

መስከረም ፩ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን  

ብጹዕ አቡነ አብርሃም የአዲ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ
መስከረም ፩ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም  

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን

በሀገራችን በኢትዮጵያ በአለንበት ሀገር በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በመላዉ ዓለም የምትገኙ በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኛችሁ እና ኢትዮጵያዉን ወገኖቼ በሙሉ፤ ከሁሉ አስቀድሞ እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደዘመነ ማቴዎስ አሸጋገራቹሁ፤ በአለፈዉም ዓመት በረድኤት ጠብቆ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ እያልኩ አዲሱ ዓመት የፍቅርና የደስታ የሰላምና የአንድነት የዕዉቀትና የብልጽግና የሕይወትና የጤና ዘመን ይሆንላችሁ ዘንድ ፈቃደ እግዚአብሔር ይሁን በማለት ልባዊ ምኞቴን በሀገረ ስብከቱ ስም ስገልጽ በታላቅ ደስታ ነዉ።

ዓመት በዓሎችህን አድርግ፡  ትንቢተ ናሆም ፩፡ ፲፭

ነቢዩ ናሆም በትንቢት መጽሐፉ ዓመታዊ በዓል ማክበር እንደሚገባ እንዲህ ሲል ያዝዛል “እነሆ የምሥራችን የሚያመጣ ሰላምንም የሚያወራ ሰዉ እግር በተራሮች ላይ ነዉ። ይሁዳ ሆይ አጥፊዉ ፈጽሞ ጠፍቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ በአንተ ዘንድ አያልፍምና ዓመት በዓሎችህን አድርግ ስዕለቶችህን ክፈል” የሚለዉን ቃል መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያናችን  መንፈሣዉያን ልጆቿ በቃል ኪዳን ጸንተዉ ሥርዓትን ጠብቀዉ  በዓላትን  እንዲያከብሩ ፤ ስለፈጣሪነቱ ፤ስለመግቦቱ፤ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ ታስተምራለች። አጥፊዉ ፈጽሞ ጠፍቶአልና እንደተባለ ስዉና እግዚአብሔር የተለያዩባቸዉ የሰቃይና የመከራ ዘመናት አልፈዉ የምህረት የይቅርታ ዓመታት መተካታቸዉን ትመሰክራለች። ከዚህም በመነሳት አባቶቻችን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የቸርነቱን ሥራ የሠራባቸዉን በባለሟሎቹ አድሮ ገቢረ ተአምራት ያደረገባቸዉን ዕለታትና ዓመትታት በወቅታቸዉና በጊዜያቸዉ አክብረዋል። እኛም ልጆቻቸዉ ፈለጋቸዉን ተከትለን በዓላትን በማክበር ክብርን እናገኝ ዘንድ ትዉፊትን ከነሥርዓቱ ሕግን ከነቀኖናዉ  ጠብቀዉ አስረክበዉናል።ከምናከብራቸዉ በዓላቶችም አንዱ ዛሬ የምናከብረዉ የዘመኑን መለወጫ ምክንያት በማድረግ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት የቅዱስ ዮሐንስ ዕለት ነዉ።

ይህ ዓዉደ ዓመት እንደሀገራችን ኢትዮጵያ አቆጣጠር ክረምትና በጋ የሚፈራረቁበት ጨለማዉ ፤ጉሙ ፤ጭጋጉ፤ አልፎ የፀሐይ ብርሃን ሞቅ ደመቅ ብሎ የሚታይበት ተራሮች ኮረብቶች የተለያዩ ህብረ ቀለማት ባሉአቸዉ አበቦች ፈክተዉ አሸብርቀዉ የሰወችን ዓይን የሚማርኩበት፤ የእግዚአብሔር ጥበቡ መግቦቱ የሚደነቅበት፤ብሔራዊ የሆነ ዐቢይ በዓላችን ነዉ፡፡ ምንም እንኳ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየሰማያት ወርዶ ድኅረ ዓለም ከቅድስተ ቅዱሳን ከድንግል ማርያም የተወለደበት ዕለትና ወርኅ ወርሀ ታህሣሥ ቢሆንም አበዉ ጊዜን በማሳሳብ ከወቅት ጋር በማገናዘብ የመስከረም ወርህ የዓመቱ መጀመሪያ እንዲሆን ወስነዋል። ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ የሚለዉ የቀደመዉ ዘመን መጠሪያ ስም ተሰርዟል።  “የተወደደችዉንም  የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል” እንደተባለ፤ኢሳ ፷፩፡ ፩-፫  ሉቃ ፬፡፲፯ ትንቢት የተነገረለት ሱባዔ የተቆጠረለት ጌታችን እና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ዓመተ ምሕረት ተቆጠረ። ከዚህም በመነሳት እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ይህ ዘመን በወንጌለ መንግሥቱ ሰባክያንና ጸሕፍያን በአራቱ ወንጌላዉያን ስም ታወቀ፡ በጌታችን በአምላካችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ዓመተ ምሕረቱ ተረጋገጠ፡ ለድሆች የምሥራች ወንጌል ተሰበከ፤ለታሰሩት መፈታት፡ ለዕዉራን ማየት፡ተሰጠ፡ ለተጠቁት ነፃነት፡ ተገኘ፤በአጠቃላይ የምሕረት የድኅነት ዓመት እንደመሆኑ ክርስቲያኖች ሁሉ ከልዩ ልዩ ወገኖቻችን ጋር በፍቅርና በሰላም በጋራ ልናከብረዉ የሚገባ በዓል ነዉ።

የተከበራችሁና የተወደዳችሁ ወገኖቼ

በዓሉን ስናከብር ልናነሳው የሚገባ ጥያቄ አለ እሱም ነቢዩ ሚክያስ እንደአስተማረን “ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልምጣና በልዑል አምላክ ፊት ልስገድ? የሚቃጠለዉን መሥዋዕትና የአንዱን ዓመት ጥጃ ይዤ በፊቱ ልምጣን?” ይላል። ሚክያስ ፮፡፮ እኛም በዓላትን በአከበርን ቁጥር ልንጨነቅበት የሚገባ ጥያቄ ቢኖር ይህ ነዉ።የዕለቱ ሞቅ ደመቅ በሥጋዊ ምኞት እና ፈቃድ ከእግዚአብሔር የሚለይ ከሆነ ለእኛ ምናችንም አይደለም፡ ቁም ነገሩ በዓሉን ምክንያት አድርጎ  ከበዓሉ ጋር የሚዛመድ መልካም ሥራ ለመሥራት ራስን ማዘጋጀቱ ነዉ።ለጥያቄዉም መልስ ለመስጠት እግዚአብሔር ከእኛ የሚሻዉ የሚቃጠል መሥዋዕት አይደለም የአንድ ዓመት ጥጃም አይደለም ከላይ በተጠቀሰዉ ምዕራፍ ቁጥር ፰ ላይ ነቢዩ እንደነገረን “ሰዉ ሆይ መልካሙን ነግሮሀል እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻዉ ምንድን ነዉ? ፍርድን ታደርግ ዘንድ ምሕረትንም ትወድ ዘንድ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” ይለናል። ወገኖቼ በዚህ ቃል መስተዋትነት የአለንበትን ዘመን ስንመለከተዉ ይቅርታ ማድረግ የሚለዉ ቃል ከሰማይ ርቋል ጥላቻ ዉዝግብ ከነጓዙ በሰዉ ላይ ስልጥኗል፡ ሁሉን ትቶ ራስን አዋርዶ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መመላለስ እንደሞኝ አስቆጥሯል። በአብዛኞቻችን ላይ ከፈቃደ ነፍስ ይልቅ ፈቃደ ሥጋ ነግሧል፡እዉነት መናገር እዉነት መሥራት እንደበደል ተቆጥሯል። ስለዚህ አሮጌዉ ዓመት አልፎ አዲሱን ዓመት ስናከብር ከእንዲህ ዓይነቱ ደዌ ለመገላገል “ምን ይዤ ወደ እግዚአብሔር ፊት ልቅረብ” ለሚለዉ ቃል እንደ አበዉ ብሂል እድሜ ለንስሐ ዘመን ለፍሥሐ ነዉና ንስሐ በመግባት በጎ ሥራ    በመሥራት የተቸገሩትን በመርዳት የተጣሉትን በማስታረቅ በዓሉን ልናከብረዉ ይገባል።   “ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” የሚለዉን ቃለ እግዚአብሔር በምስማት  ክርስትያናዊ ሕይዎታችን በትሕትና የተመላ በፍቅር የታነፀ ሊሆን ግድ ይላል። 

አባቶቻችን የቃሉ ታዛዦች ሁነዉ ሕግንና ሥርዓትን ጠብቀዉ ከራስ ወዳድነት ርቀዉ ፍቅረ እግዚአብሔርን ፍቅረ ቢጽን በሥራ ተርጉመዉ አሳይተዉናል።ስለሆነም  የአባቶቻችንን ፈለግ በመከተል በአሉን እንደምናከብር ሁሉ ትሕትናን ገንዘብ አድርገን ልዩነትን አርቀን አንድነትን መርጠን  በአንድ ሀሳብ ተስማምተን  ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀን ርትዕት በሆነችዉ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሀይማኖታችን ጸንተን በተሰጠን የንስሐ ዓመት እንጠቀምበት

በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኛችሁ በሙሉ

አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን ስንባባል ምንጊዜም ልናስታዉሰዉ የሚገባን መርሳት የሌለብን አንድ ነገር አለ ይህዉም የበደለ ይቅርታ የማይጠይቅበት ንስሐ ገብቶ ወደ እግዚአብሔር የማይቀርብበት አዲስ ዓመት ለአንድ ሰዉ ትርጉም የሌለዉ መሆኑን ነዉ።ይህንም በተመለከተ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ በምሳሌ እንዲህ ሲል ያስተምረናል “የወይን አትክልት ሠራተኛዉንም እነሆ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም ቁረጣት ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጎሳቁላለች አለዉ “ይላል።ሉቃ ፲፫፡፯ ከዚህም የምንማረዉ ያለምልካም ሥራ ዓመታት ማስቆጠር ዉድቀትን የሞት ሞትን እንጂ ክብርን እና ትንሣኤን አያመጣም አያስገኝምም።ሦስት ዓመት ሙሉ በለሷ ፍሬ ባለመስጠቷ መሬቱን እንዳታጎሰቁል ለአትክልተኛዉ ቆርጠህ ጣላት የሚል ትእዛዝ መሰጠቱን አይተናል፡ በዚህ አንፃር እያንዳንዳችን ራሳችንን ስንጠይቅ ሦስት ዓመት አይደለም በሦስት ዓመት የምናባዛዉ በብዙ የሚቆጠሩ ዓመታት ተሰጥተዉናል።ስለዚህ እንደሥራችን ያይደለ እንደቸርነቱ ያለምንም ዋጋ በሰጠን ዓመታት ምን ሠራንባቸዉ? ዛሬስ ምን መሥራት አለብን? በማለት የትናትን በደል የማይቆጥር መመለሳችንን እንጂ መጥፋታችንን የማይፈልግ አምላክ ነዉና በአዲሱ ዓመት በሙሉ ልባችን ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ። 

በተጨማሪም ሁላችንም በአንድነት ልናስብበት እና ልንጸልይበት የሚገባን ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በተመለከተ ነዉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሺ ለተቆጠሩት ዓመታት አንድነቷን ጠብቃ ከራሷም አልፎ የሀገር የወገን አንድነት አስጠብቃ ዘመናትን ማሳለፏ የተረጋገጠ ሀቅ ነዉ። ዛሬ ደግሞ በአለንበት ዘመን በምንኖርበት በዉጩ ዓለም ነገሮች እንደዋዛ እየተጀመሩ አንዳንዶቻችን በራስ ወዳድነት በፈጠርነዉ ልዩነት የቤተ ክርስቲያን አንድነት ፈተና ላይ ወድቋአል።ሁሉም የየግሉን ሩጫ ጀምሯል። ስለዚህ በነቢዩ ዘካርያስ እንደተነገረን “የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቆጣሀቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸዉ እስከመቼ ነዉ? አለ እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረዉ መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረዉ፡” ዘካ ፩፡ ፲፪   

የተከበራችሁ አባቶቼ እና እናቶቼ ውንድሞቼ እና እህቶቼ 

ቤተ ክርስቲያናችን በእዉነተኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ አንድነቷን ጠብቃ የኖረችዉን ያህል በኛ እንዳታፍር የቤተ ክርስትያን ልዩነት ጠፍቶ አንድነት ሰፍኖ የእገሌ ወእገሌ መባባሉ ቀርቶ በሚያጽናና ቃል ለአንድ ዓላማ ከጥላቻ ከክርክር ከማይጠቅም ነገር ራሳችንን እንለይ።የማይጠቅመዉን አሮጌዉን ነገር ከአሮጌዉ ዓመት ጋር ወደኋላ ጥለን በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንፈስ ስለእዉነትና ስለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት ሁላችህንም ጠበቆች እንሁን ።አዲሱን ዓመት የሰጠን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።በዓሉን በሰላም በፍቅር በመተሳሰብ በመረዳዳት እንክብር፡ መልካም ዘመን ለሁላችሁ፡ ይሁን። አሜን።

 

አምላካችን እግዚአብሔር ለሀገራችን ለኢትዮጵያና ለዓለም ሁሉ ሰላምን ይስጥ።

ሁላችንንም እግዚአብሔር ይባርከን።

 

አባ አብርሃም

ሊቀ ጳጳስ

Home| Feedback| Webmaster
EOTC-DC Diocese., All Rights Reserved