በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከአንድ ዓመት በላይ በትጋት ሲሠራበት የነበረውን የመንበረ ጵጵስና ግዢ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በድንግል ማርያም አማላጅነት በአባቶችና በምእመናን ትጋትና ርብርብ ተግባራዊ ሊያደርግ መቻሉን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም አበሰሩ። በትንሣዔ ማግስት፣ በቅ/ሚካኤል ወርሃዊ በዓል መታሰቢያ ዕለት እና በማዕዶት ቀን ይህ ታላቅ ዜና መሰማቱ በአገልግሎቱ የተሳተፉትን በሙሉ ከልብ አስደስቷል።
በቃለ ዐዋዲ ዐንቀጽ አርባ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ እንደ ተገለጠው «የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያትና ለወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለው” እና በአንድ የተወሰነ ክልል ቤተ ክህነቱን ወክሎ የሚሠራ ተቋም ሲሆን፣ ሃይማኖቱን እና ቀኖናውን ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ፣ ከሐዋርያት ጀምሮ የመጣውን ሀብተ ክህነት ለመጠበቅ እና ለማስተላለፍ፣ ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ፣ ገዳማት እና አድባራት እንዲረዱ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተከሉ፣ ምእመናን ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ መብት እንዲከበር፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ወጥ እና ሥርዓቱን የጠበቀ እንዲሆን፣ የካህናት አስተዳደር እና አገልግሎት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ መሠረት እንዲሆን፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት እና ንብረት በሕግ እና በሥርዓት መሠረት እንዲጠበቅ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያኒቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ እና እንዲሰጡ ያደርጋል