በመሥራች ኮሚቴው እና አባላቱ ከፍተኛ ጥረት በፈቃደ እግዚአብሔር “የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን” በሆነው በበዓለ ጰራቅሊጦስ ቀን በቨርጂንያ (115 ዋሽንግተን ስትሪት አሌክሳንደሪያ ቨርጂንያ) ተከበረ።
በቅዳሴ ቤቱ አከባበር ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፣ ቁጥራቸው የበዛ ምእመናን እና ምእመናት ተገኝተው መንፈሳዊ ደስታቸውን በዕልልታና በጭብጨባ አስተጋብተዋል።
ብፁዕነታቸው በክብረ በዓሉ ለተገኙት ምእመናን በአስተላለፉት ቃለ ምእዳን እና ቡራኬ “በሀገረ ስብከቱ የተመሠረተው የመንበረ ጵጵስናው ቤተ ክርስቲያን፤ ሥርዓትን ጠብቆ የተመሠረተ“ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህም ባሻገር “የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፤ ቀኖናና ትውፊት ሳይከለስና ሳይበረዝ ለነገው ተተኪ ትውልድ ለማስተላለፍ እና ለማስረከብ መንፈሳዊ ግዴታ” ያለብን መሆኑን በአጽንዖት ገልጸው “መለያየትን እና መመከፋፈልን ለማስወገድ ይልቁንም የተለያየን አንድ ሆነን የተጣላን ታርቀን የቤተ ክርስትያናችንን ህልውና ጠብቀን ለትውልዱ ማቆየት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ከመሆኑም በላይ በመለያየትና በመከፋፈል አንድነትን ማምጣት የማይቻል” መሆኑን አስረድተዋል።
ብፁዕነታቸው ከዚህ በማያያዝ “በመቀራረብና በመመካከር ለችግሮች መፍትሄ በመፈለግ የእናታችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ህልውና እንዲጠበቅ፤ ቤተ ክርስቲያናችን የወላድ መካን በመሆን ሀዘንተኛ እንዳትሆን፤ ውድቀቷን ለሚፈልጉ ተቃዋሚዎቿ እንዳትጋለጥ፤ ጉዳዩን በቸልተኛነት ማየት የለብንም” ብለዋል።
በመጨረሻም “የታሪክ ተወቃሾች እንዳንሆን ልጆችሽ አለን በማለት የሕጓ ጠባቂዎች፣ የሥርዓቷ ፈጻሚዎች እንድንሆን ቤተ ክርስቲያን የእናትነት ጥሪዋን ታስተላልፋለች” ሲሉ ብፁዕነታቸው ለሁሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። በሌላ መልኩም ሀገረ ስብከቱ በማኅበራዊና መንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ ካህናትን እና ምእመናንን በማስተባበር የሚሠራ እና የሚያሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህ መልክ ከሌሊት የተጀመረው አገልግሎት ታቦተ ሕጉ ዑደት አድርጎ ከገባ በሁዋላ በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል።
|